Published On: Sun, Jan 8th, 2017

አንድ ለመንገድ ( One For The Road )

ለዛሬው ጽሁፌ መነሻ የሆነኝ ምክንያት ባለፈው ሀሙስ ማለትም በ 05/01/2017 ብራስልስ ከሚገኝ ከአንድ መ/ቤት ቀጠሮ ስለነበረኝ ወደዚያው
ተጉዤ ነበር ፤ የሄድኩበትን ጉዳይ ጨርሼ ስወጣ ከዘጠኝ አመት በፊት ለአንድ አመት የኖርኩባትን የብራስልስ ከተማ ውበትንና ለውጥ እንዲሁም
ከነዚህ አመታት በሁዋላ ምን ለውጥ እንዳላት ለማየት እና እንዲሁም የሚጠብቀኝን ረጅም የባቡር ጉዞ እንዳይሰለቸኝም ጭምር በማለት እግሬን
ለማፍታታትና ትንሽም ዞር ዞር ብዬ ለማየት እንዲረዳኝ ወደከተማዋ ሴንተር የሚወስደውን መንገድ ይዤ መጉዋዝ ጀመርኩ ፤ በመንገዴ ላይ
የማያቸው አዳዲስ ነገሮች ካሉ በማለት እየቃኘሁ ስጉዋዝ ሳለ ከወደ ሁዋላዬ ተደጋጋሚ የጥሪ ድምጽ ሰማሁ ጥሪው ለማን እንደሆነ ባላውቅም ለኔ
እንዳልሆነ ግን እርግጠኛ ነበርኩ ከዚያም በላይ የኔ ስም ባለመሆኑ መለስ ብሎ ማየት አላስፈለገኝም እናም በውስጤ ይህን ያህል ጊዜ እየተጠራ
የማይሰማ ሰው ደንቆሮ ሰው መሆን አለበት አልኩኝ ለራሴ ፤ ይሁን እንጂ ድምጹ እየራቀኝ ቢሄድም አንድ ከፊት ለፊቴ የሚመጣ ሰው ሚስተር
ብሎ በጣቱ ወደ ሁዋላዬ ጠቆመኝ ሰውዬው ወዳሳየኝ አቅጣጫ ዞር ብዬ ስመለከት አንድ በመካከለኛ የሰውነት አቁዋም ላይ ያሉ አዛውንት እጃቸውን
እያወዛወዙ ምልክት ሰጡኝ የጠሩኝን ሰው ማንነት ባላውቅም ለምን እንደጠሩኝ ለማወቅ ወደሳቸው ስሄድ በመደነቅ አይነት ፈገግታ ማማሚያ እኔ
አላምንም አሉ በሚገርም ፈገግታ ተሞልተው ፤ ማንነታቸውን ለማስታወስ ስለከበደኝ ግር በተሰኘና በተጠራጠረ እይታ ሳያቸው
”ሉቻኖ ” እኔ ነኝ እኮ አሉኝ በፈገግታ ሳቅ  ብለው ፤ማንነታቸውንና ስማቸውን በቶሎ ማስታወስ ቢከብደኝም በዚህ ስም ሊጠራኝ የሚችል
አንድ ሰው ብቻ ነው ይህም ሰው ጎረቤቴ የነበሩት ጣሊያውያኑ አዛውንት ! ማንነታቸውን ለማስታወስ ጊዜ መውሰድ ባያስፈልገኝም ከፊቴ ቆመው
የማያቸው ሰው ግን በመልክም ሆነ በቁመና ቀድሞ ከማውቃቸው ሰው በጣም የተራራቁ ናቸው : ከቀድሞው ማንነታቸው ያልተለወጠው እና በቀላሉ
እንዳስታውሳቸው የረዳኝ ይጠሩኝ የነበረውን ስም መጠቀማቸው እና ፈገግታቸው ነበር
እናም በሃሳብ ዘጠኝ አመት ወደ ሁዋላ በመሄድ ስማቸውን ለማስታወስ ሞከርኩ በመቀጠልም መሲ ዶን አልኩኝ በመገረም ስሜት ሆኜ ፤
እኚህን የእድሜ ባለጸጋ የሆኑትን ሰው ሳውቃቸው ጺም አልባ እና ወፍራም የነበሩ ሲሆን አሁን ግን ባለ ረጅም ጺም ከመሆናቸውም በላይ መነጽር
አድርገው ሳገኛቸው ፈጽሞ ሌላ ሰው ሆኑብኝ : እሳቸው አውቀውኝ ባይጠሩኝ ኖሮ እኔ ፈጽሞ ላውቃቸውም ሆነ ላስታውሳቸው ባልቻልኩም ነበር
ሉቻኖ የሚለውን ስም የሰጡኝ ከሳቸው ጋር በተገናኘሁ ቁጥር ብዙውን ጊዜ ስለ እስፖርት ስለምናወራ በተለይም በዝና ስለማውቃቸው ሁለት ታዋቂ
የቀድሞ ብሄራዊ ቡድናችን ተጫዋቾች ስለነበሩት ወንድማማቾች ሉቻኖ ባሳሎ እና ኢታሎ ባሳሎ ታሪክ እና ዝና የሰማሁትን በስሜት ሆኜ ሳወራቸው
በመገረም ወትሮም በአንድ ነገር ላይ ሲመሰጡ እንደሚያደርጉት ሁሉ ጸጉራቸውን ሲዳበሱ ቆይተው
ጋደኞችህ ነበሩ በማለት ጠየቁኝ እኔም አይደሉም ስላቸው
ቀበል አድርገው አሃ ገባኝ በደንብ ታውቃቸው ነበር ማለት ነው አሉ
ይሄ የምነግሮት ሁሉ የሰማሁትን እንጂ እንዚህን ተቻዋቾች እንኩዋንስ  ጨዋታቸውን ምን እንደሚመስሉ እንኩዋን አይቻቸው አላውቅም ስላቸው
ማማሚያ ጨዋታቸውንም ሆነ በአካል ምን እንደሚመስሉ እንኩዋን አይተህ የማታውቃቸውን ተጫዋቾች በደንብ እንደምታውቃቸው ሆነህና ልክ
ትናንት እንደተደረገ ሁሉ እንደዚህ ተመስጠህ ስታወራኝ በጣም ነው የገረመኝ አሉ በማያያዝም አንተ ልክ እንደ አጎቴ በኩዋስ ፍቅር የተለከፍክ ነህ
እንዲያውም ስምህን ለመያዝም ሆነ ለመጥራት ስለሚያስቸግረኝ እንዲሁም የእህቴ ልጅ ስሙ ሉቻኖ ስለሆነ ቅር ካላለህ ከዛሬ ጀምሮ ለኔ ሉቻኖ ነህ
አሉ እናም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከተለየኋቸው ጊዜ ድረስ በዚህ ስም ይጠሩኝ  ነበር እኔም በተፈጠረው አጋጣሚ በጣም ተደንቄ ሳስተውላቸው
ትውስታቸው በቅጽበት ውስጤን ሞላው በጣም የሚጋርመው ነገር እኔም ብሆን ሙሉ ስማቸውን በትክክል ለመጥራት ስለሚያስቸግረኝ በቅጽል
ስማቸው ዶን አልኩኝ በድጋሜ በፈገግታ ተሞልቼ ፤ከዚያም ኮሜስታ በቤኔ አልኩዋቸው በማውቃት ጣልያንኛ ፤
እሳቸውም ደህና ነው አሉኝ ሁሌም እኔን ሲያገኙ በሚጠቀሙባት አማርኛ ፤
ሰላምታ ከተለዋወጥንና ትንሽ እያወራን ከተጉዋዝን በሁዋላ የከተማዋ ሴንተር አካባቢ በመድረሳችን ቡና ለመጠጣት እና ትንሽም ለመጨዋወት
ከአንድ ሆቴል ገባን ቀድሞ ሳውቃቸው ኮርነር ላይ ካልሆነ በስተቀር እንደማይቀመጡ ስለማውቅ የሚወዱትን የመቀመጫ ኮርነር አካባቢ በአይኔ
ሳማተር ምን እየፈለኩ እንደሆነ ስለገባቸው አይ ሉቻኖ ከስንት አመት በሁዋላም ቢሆን አልረሳህም አሉ በፈገግታና በመገረም ቀጥሎም አይዞህ
የትም መሆን እንችላለን ብለው መሃል ላይ ካለው ባዶ ወንበር እንደተቀመጥን አንተ ከዚህ ከሄድክ በሁዋላ ለበርካታ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ሄጄ
ነበር ሆኖም ግን ሁሉም ነገር ስለተለዋወጠ ባለፈው አመት ለመጨረሻ ጊዜ ስሄድ ለሶስት ወር ቆይታ ለማድረግ ነበር ሆኖም ግን እዚያ ከሚኖሩት
የሰማሁት እና በአይኔም ያየሁት ሁኔታ ስሜቴን ስለጎዳው የቆይታ ጊዜዬን ለውጦት ወር ሳይሞላኝ ተመለስኩ አሉኝ በማዘን ፤
ምን ነው አልኩዋቸው ስሜታቸውን የጎዳውን ነገር ለማወቅ ፤
አዬ ተወው ባክህ አሉኝ ትክዝ ብለው ፤
አልፎ አልፎ በስልክም ሆነ ከሰው የምሰማው አስከፊ የሰቆቃ ኑሮ ለኔ አዲስ ባይሆንም ከሳቸው አንደበት ግን ልክ አዲስ ነገር እንደተፈጠረ ሁሉ
ለመስማት በመጉዋጉዋት አረ ይንገሩኝ እንጂ ዶን ምን ቢያዩና ቢገጥሞት ነው ስሜቶ እንዲህ የተነካው አልኩዋቸው ከበፊቱ በበለጠ በጉዋጉዋ
ስሜት ሆኜ
ምላሻቸው ግን በትካዜ የተሞላ ዝምታ ነበር
ቀደም ሲል እዚህ በነበርኩበት ወቀት ሁሌም ምኞታቸው እና ህልማቸው ጡረታ ሲወጡ ኢትዮጵያ ሄደው ክረምት ከበጋ ጸሃይ እየሞቁ ቀሪውን
እድሜያቸውን እዚያ ለመኖር እንደሚፈልጉ ያጫውቱኝ ስለነበር በአመት ቢቻል ሁለቴ አልያም አንድ ጊዜ እንደሚሄዱ ያጫውቱኝ ነበር እናም
እዚህ በነበርኩበት ወቅት ሁለት ጊዜ መሄዳቸውን ባውቅም እስከ አሁን ቢያንስ ቢያንስ ከስምንት ጊዜ በላይ ሊሄዱ እንደሚችሉ ለመገመት ሞከርኩ
እናም እንደዚያ የሚወዷትንና ሊኖሩባት የተመኟትን ሃገር ተስፋ የሚያስቆርጥ ምን አይነት ነገር ቢገጥማቸው ነው ያዘኑት ብዬ ለማወቅ ቸኮልኩኝ
እናም ረጋ ብዬ ምን ገጠሞት ዶን አልኩዋቸው ?
ምን ብዬ ልንገርህ ሁሉም ነገር ተበላሽቶአል አሉኝ
በመቀጠልም የመጨረሻዬ በሆነው የአጭር ጊዜ ቆይታዬ አንድ በጣም የምጠላውንና ማስታወስም የማልፈልገውን ነገር እንዳስብ አደረገኝ አሉ
ምን አልኩዋቸው ሙሉ አቴንሽን ሰጥቼአቸው
አየህ ያኔ እዚህ በነበርክበት ወቅት ይህን ሀገር እና ጣልያንን በማወዳደር እንዲሁም ወደዚህ ሀገር ለምን እንደመጣሁ ስትጠይቀኝ ጉዋደኛዬን ተከትዬ
መጣሁ ያልኩህ እውነት ቢሆንም ለመምጣቴ ዋናው ምክንያት ግን ሌላ ነበር ይህም ቀደም ሲል እንደነገርኩህ ተወልጄ ያደኩት በሲሲሊ
ውስጥ ከሚገኝው ከፓሌርሞ ከተማ ወጣ ብላ ከምትገኝ ትንሽዬ ከተማ ነው: እንደ አሁኑ ነገሮች ሳይሻሻሉና ሳይለወጡ  በዚያን ዘመን
በዚህች ከተማ ውስጥ ብዙ ነገሮች በማፍያ ሰዎች ስለሚካሄድ እዚያ ከኖርክ ምንም ነገር ብታይ እንዳላየ ሆነህ አንደበትህንና አይንህን
ቆጥበህ ነው መኖር ያለብህ ደግሞም ማን ምን እንደሆነ ስለማይታወቅ በሁሉም ነገር ቁጥብና ጥንቁቅ መሆን አለብህ ፤ እናም የአጋጣሚ
ጉዳይ ሆኖ የአባቴ ወንድም (አጎቴ) በስህተት ከሰው ጋር ይጣላል የተደባደበው ሰው ክፉኛ ይጎዳና ሆስፒታል ይገባል
ከዛሬ ነገ ከጉዳቱ አገገሞ ይወጣል ተብሎ ሲጠበቅ ሳይድን ቀርቶ በዚያው ይሞታል እናም ይኸው አጎቴ ከጸቡ በሁዋላ የተጣላውን ሰው ማንነት
እና የማን ዘመድ እንደሆነ ሲሰማ ወደቤቱ ሳይመለስ በዝያው ከአካባቢው ይጠፋል
በመሰወሩ የተበሳጩት የተጎጂ ቤተሰቦችና ዘመዶች ፍለጋውን በሚስጢር ቢያጥዋጥፉትም ሊያገኙት አልቻሉም ይህ ሁኔታ ያላማረው እና
ያስጨነቀው አባቴ ግራ ቢገባውና የሚያደርገው ቢጠፋው አማላጅ ልኮ ስለ ወንድሙ ምንም እንደማያውቅ እና ወዴት እንደሄደ እንኩዋን
ምንም ፍንጭ እንደሌለው በአማላጆቹ በኩል ገለጾ ስለቤተሰቡ ደህንነት ምህረትን ቢጠይቅም ያገኘው ምላሽ ግን ይህ ጉዳይ በፍርድ ቤት
የተያዘና የሚታይ ስለሆነ እኛ አንተንም ሆነ ወንድምህን ለመኮነንም ሆነ ምህረት ለመስጠት ምን ቤት ነን !ስለዚህ የወንድምህን ጉዳይ
በፍርድ ቤት ተከታተል ብለው ለማማለድ በሄዱት ሽማግሌዎች በኩል መልስ  ይልኩለታል የዚህ መልስ ትርጉም የገባው አባቴ ለጉዋደኛዬ
ቤተሰቦች ስልክ በመደወል እኔን ከልጃቸው ጋር ወደዚህ እንድመጣ ሲልከኝ መስቀል እና መጽሀፍ ቅዱስ ላይ እጄን አስጭኖኝ በምንም
ምክንያት ቢሆን ወደዛ ሃገር እንዳልመለስ ቃል አስገብቶኝ ነበር የተሰናበተኝ  እናም እኔ ወደዚህ በመጣሁ በሁለተኛው ሳምንት በመኪና
አደጋ ሞተ የሚል አሳዛኝ ዜና ደረሰኝ  ይህ ሁኔታ በዚህ ሳያበቃ ከሶስት ወር በሁዋላ ደግሞ አጎቴ ከአንድ ሆቴል ክፍል ውስጥ ሞቶ ተገኝ
የሞቱ ምክንያት ድንገተኛ የልብ ድካም ነው ተብሎ ተነገረ ከአጎቴ ሞት በሁዋላ ወደዚያ እንዳልመለስ የአባቴ የአደራ ቃል ያዘኝ ሁሌም
እሱን ባስታወስኩት ቁጥር ስንለያይ የተናገረኝን ምን ጊዜም አልረሳውም አየህ ልጄ አጎትህ በሰራው ነገር እኔም ሆንኩ ቤተሰባችን
ተወቃሽም ሆነ ተጠያቂ መሆን አይገባንም ነበር ይባስ ብሎ ምንም የማናውቀውን እኛን ለመጉዳት ማሰብ ትልቅ ስህተት ነው
”በመስታወት ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ዲንጋይ አይወራወሩም ” እንደሚባለው ሁሉ ከዚህ በሁዋላ ድንጋይ መወራወር መጀመሩ
አይቀሬ ነው እና ምንም ነገር ተፈጥሮ ብትሰማ ፈጽሞ ወደዚህ ለበቀል እንዳትመለስ በማለት ቃል አስገብቶና አስምሎ ላከኝ እኔ
ወደዚህ ስመጣ ትንሽ ልጅ ነበርኩ እናም አጎቴ በሰራው ስህተት የተነሳ ከኛ ቤተሰብ አባቴን ጨምሮ ስምንት ሰው ሲገደል፣ ከነዚያም
ወገን ደገሞ ሶስት ሰው ሞትዋል እኔም ወደዚያ እንዳልመለስ ላባቴ ቃል በገባሁት መሰረት ይኽው ዘመኔን እዚህ ጨረስኩት ብለው ሲቆዝሙ
ይቅርታ ዶን በአጎቶ ጥፋት እንዴት ይህ ሁሉ ቤተሰብ ሊያልቅ ቻለ አልኩዋቸው
በቀል ነዋ ቬንዴታ አሉ ስብር ባለ የድምጽ ቃና! በማያያዝም አባቴ ለሰው ችግር ደራሽ እና ርሁሩህ ከመሆኑም በላይ በአካባቢያችን በጣም
ተወዳጅ ሰው ነበር እኔንም በዚህ ባህሪ ነው ቀርጾ ያሳደገኝ ለዚያም ነው ወደዚህ ስመጣ ምንም ነገር ቢፈጠር እና ብሰማ ለበቀል እንዳልነሳና
ወደዚያ እንዳልመለስ ቃል ያስገባኝ እናም እኔ ከአካባቢው መሰወሬ ሲታወቅ በአንድ በኩል አማላጅ እየላከ በሌላ በኩል ወንድሙንም
ያሸሸውና ትልቁን ሚና እየተጫወተ ያለው እሱ ነው በማለት ማንነቱ በማይታወቅ ሰው በመኪና ተገጭቶ እንዲሞት ተደረገ ይህ ድርጊት
ብዙዎችን ያሳዘነ ቢሆንም ይበልጥ ግን ዘመዶቼን በጣም ከማስቆጣቱ በላይ ጥፋተኛውን እንደመበቀል ምንም የማያውቀው አባቴ የዚህ
ሰለባ በመሆኑ የተበሳጩት ዘመዶቻችን ደግሞ የበቀል ምላሽ ያደረጉት የዋናውን መሪ ልጅ በመግደል ነበር እንዲህ እያለም ያን ያህል ሰው
በከንቱ አለቀ እናም በኢትዮጵያም ያየሁት እና እዚያ እንዳልቆይ ያደረገኝ እና ያስጠላኝ ይህንኑ አይነት ተመሳሳይ ድርጊት ስላየሁ እና
ስለሰማሁ ነው አሉኝ
ምን አዩ ምንስ ሰሙ አልኩዋቸው ?
በአሁኑ ሰአት በኢትዮጵያ ውስጥ በመንግስት ስም እየተደረገ ያለው ነገር በጣም የሚያሳዝን እና የሚያስጠላ ነው የእነሱን አስተዳደር እና
ፖለቲካ የሚቃወም እና የማይደገፍ ሁሉ እንደ ልዩ ጠላት ተደርጎ በመታየቱ ሲታደን እሱን ካላገኙት ደግሞ በሱ ፈንታ ምንም የማያውቁትን
ቤተሰቦቹንና ዘመዶቹን ማንገላታት ብሎም የደረሱበት መጥፋት በጣም ትልቅ ስህተት ነው እስቲ እንደ ምሳሌ እንውሰድና ባለፈው አመት
በአሜሪካ ውስጥ ምን እንደተረገ ላስታውስህ; በየጊዜው በርካታ ጥቁሮች በጸጥታ ሃይሎች ተገደሉ ሲባል በዜና እንሰማ ነበር ይህ ሁኔታ
መለኩን ቀይሮ በስውር አልሞ ተኩዋሽ(ስናይፐር) የመልሶ ማጥቃቱ እርምጃ በመጀመሩ ስንት ፖሊሶች ናቸው በከንቱ የተሰዉት ስንትስ
ልጆች ናቸው ወላጅ አልባ የሆኑት ስንትስ ቤተሰብ ነው የተበተነው እና ያዘነው እናም የደረሰውን ጉዳት ቤት ይቁጠረው እንጂ በቁጥር
ላሰላልህ አልችልም!አየህ በትንሽ ጥፋት የተነሳ እጃቸው ምንም የሌለበትን ንጹሃንን ማሰቃየት እና ከአይን ሰውሮ ህይወት ማጥፋት ትልቅ
ስህተት እና አሸናፊ የሌለበትና የማይቆም ጦርነት ነው ይህ ደግሞ ለማንም አይበጅም ደግሞም አትርሳ የትም ይሁን የትም ሁላችንም
በመስታወት ቤት ውስጥ ነው የምንኖረው አሉኝ እናም ይህን የማያስተውል ካለ ጅል ወይም እራሱን ስቶ የተኛ ሰው ብቻ መሆን አለበት
አሉኝ ግንባራቸውን ቁዋጥረው
በመቀጠልም እስቲ ወደ አንተ ልመለስ እና አረ ለመሆኑ ይህን ያህል አመት የት ጠፍተህ ነው የከረምከው አሉኝ በጥያቄ አስተያየት
ቦታ ቀየሬ ነው አልኩዋቸው
የት ብትሆን ነው ታድያ እንዲህ ከአይን የተሰወርከው አሉኝ በመገረም
የምኖርበትን ቦታ ስነግራቸው ኦ እውነትም ርቀሃል አሉኝ አይናቸውን አፍጥጠው እና ወደሁዋላቸው ተመልሰው ወንበራቸውን በመደገፍ
ታድያ ጊዜውም ሄድዋል ከዚህ በሁዋላ በምሽት ይህን ያህል እርቀት ከምትጉዋዝ ለምን እኔ ጋ ስትጫወት አድረህ ነገ ረጋ ብለህ አትሄድም
በዚያውም እኮ ልጆቼንም ታያቸዋለህ አሁን አደገው ጎርምሰዋል አሉኝ
እኔ ሳውቃቸው የመጀመሪያ ሚስታቸው በካንሰር ከሞቱ በሁዋላ ሌላ ሴት አምጥቼ ልጆቼን አላሳቅቅም በማለት ላለማግባት ወስነው
እንደነበረ አውቃለሁ አሁንስ በምን ሁኔታ ላይ ይሆኑ ይሆን በማለት ሳሰላስል ስለሁ ድምጻቸው አቁዋረጠኝ
አየህ አሉ በመቀጠል አንተ ከሄድክ በሁዋላ ብዙ ነገሮች ተለውጠዋል
አንዱና ዋናው በልጆቼ ግፊት ሌላ ሚስት አግብቼ የሁለት ልጆች አባት ሆኛለሁ እናም በዝና የሚያውቁህን በአካል ሊያዩህ ይገባል አሉኝ
ዶን የዛሬን ይለፉኝ እና በሌላ ጊዜ ብመጣ ይሻላል ብያቸው ለመሄድ ተነሳሁ
መቸም ዛሬ በዛሬ አልስጨንቅህም ሆኖም ግን በሌላ ጊዜ መጥተህ እንደምትጠይቀኝ እረግጠኛ ነኝ እናም እንግዲህ አደራ እኔና ቤተሰቤ
ምን ጊዜም የአንተን ጉብኝት በናፍቆት እንጠብቃለን ደግሞም በማንኛውም ጊዜ ብትመጣ በደስታ ልንቀበልህ ዝግጁ ነን አደራ መተህ
ጠይቀን ብለውኝ ሲሰናበቱኝ ድጋሜ የማላያቸው ይመስል ሆዴን ባር ባር አለው !
ከሳቸው ተለይቼ ወደ ባቡር ጣብያ ስገሰግስ
”ልጄ ሁላችንም በመስታወት ቤት ውስጥ ነው የምንኖረው በመስታወት ቤት ውስጥ የሚኖሩ ድንጋይ አይወራወሩም” ያሉት አባባል
በመንገዴ ሁሉ ስጋዝ በጭንቅላቴ ውስጥ ደጋግሞ ሲያስተጋባ እውነትም ሁላችንም የምንኖረው በመስታወት ቤት ውስጥ ነው አልኩኝ
ወደ ሰማይ ቀና ብዬ እያየሁ!

=> ይህን ድህረ ገጽ ለምትከታተሉ አንባቢዎቼ በሙሉ:  በግል ችግር ምክንያት በዚህ ገጽ ላይ ላልተወሰነ ጊዜ ፖስት ማድረግ
የምናቆም መሆናችንን በዚህ አጋጣሚ ከይቅርታ ጋር ለመግለጽ እንወዳለን

About the Author

አንድ ለመንገድ ( One For The Road )